የሲንጋፖር አየር መንገድ 15 ሺህ ኪሎሜትር በመብረር ረጅሙን የበረራ ሰዓት ሊያስመዘግብ ነው

Posted by

የሲንጋፖር አየር መንገድ በረራውን ወደ ኒውዮርክ የጀመረው ከአምስት ዓመታት በኋላ በድጋሚ ሲሆን፤ የመጀመሪያው በረራ ውድ ሆነብኝ ብሎ ነበር ያቋረጠው።

በረራው 15 ሺህ ኪሎ ሜትር የሚሸፍን ሲሆን፤ አውሮፕላኑ ያለምንም እረፍት ለ19 ሰዓታት ይበራል።

የአውስትራሊያው ኳንታስ አየር መንገድ በያዝነው ዓመት መጀመሪያ አካባቢ 17 ሰዓታት የሚፈጅ በረራ ወደ ለንደን የጀመረ ሲሆን፤ የኳታር አየር መንገድ ደግሞ 17.5 ሰዓታት የሚፈጅ በረራ አድርጎ ነበር።

ከቻንጊ አየር መንገድ ተነስቶ ኒውዮርክ አየር ማረፊያ መዳረሻውን ያደረገው አውሮፕላን ገና በመጀመሪያዎቹ ሰዓታት ሙሉ በሙሉ በሚባል ደረጃ መቀመጫዎቹ ተይዘዋል።

የሲንጋፖር አየር መንገድ እንዳስታወቀው በዓለም ረጅሙ በረራ የተጀመረው ያልተቆራረጠ በረራ ማድረግ የሚፈልጉ ተጠቃሚዎች ቁጥር በመጨመሩ ነው።

አየር መንገዱ ለቢቢሲ እንደገለጸው አብዛኛዎቹ የአውሮፕላኑ መቀመጫዎች ቀድመው የተያዙ ሲሆን፤ የተንደላቀቁ የተባሉት ክፍሎች ብቻ ጥቂት ቀርቷቸዋል።

ተጓዦች በአውሮፕላኑ በሚኖራቸው ቆይታ ሁለት የምግብ ሰዓቶች ይኖሯቸዋል፤ ከዚህ በተጨማሪም ጀርባቸውን አረፍ ማድረግ ሲያምራቸው ደግሞ የሚጠቀሙት ቅንጡ አልጋ ተዘጋጅቶላቸዋል።

ለበረራው ጥቅም ላይ የሚውለው አዲሱ ኤርባስ አውሮፕላን መለስተኛ ቅንጡ በተባሉ ወንበሮቹ 161 ተሳፋሪዎችን ማስተናገድ ይችላል።

የመነሻውም የመዳረሻውም ከተሞች እጅግ ከፍተኛ ንግድ የሚካሄድባቸው ቦታዎች ስለሆኑ ነጋዴዎችና በተለያዩ ስራዎች ላይ የተሰማሩ ሰዎች በደስታ ረጅሙን በረራ ይጠቀማሉ ይላል የአቪዬሽን ባለሙያ የሆኑት ጆፍሪ ቶማስ።

‘ከዚህ በተጨማሪም ሁል ጊዜም ቢሆን አዲስ በረራ ሲጀመር ተጠቃሚዎች ቁጥራቸው ይጨምራል።’

ከዚህ ጎን ለጎን ኳንታስ አየር መንገድ 20 ሰዓታት የሚፈጅ ከለንደን ሲድኒ በረራ ለማስጀመር ከአውሮፕላን አምራቾቹ ‘ኤርባስ’ እና ‘ቦይንግ’ ጋር ድርድር መጀመሩን አስታውቋል።

በተጨማሪም አየር መንገዱ አውስትራሊያን ከሰሜን አሜሪካ የሚያገናኝ ያልተቆራረጠ በረራ ለመጀመር አቅዷል።

ፍላይት ግሎባል በተባለው ጋዜጣ ዋና አርታኢ የሆኑት ማክስ ኪንግስሊ ግን ይህ አካሄድ አዋጪ ላይሆን ይችላል ይላሉ። በመጀመሪያዎቹ ወራትና ምናልባትም ዓመታት የተጠቃሚዎች ቁጥር ከፍተኛ ሊሆን ይችላል።

‘ነገር ግን ከዓለም ኢኮኖሚ ጋር በተያያዘ አንዳንድ ለውጦች ሲመጡ ተጠቃሚዎች ወደ ድሮዎቹ በዋጋ ቅናሽና የተቆራረጡ በረራዎች ፊታቸውን መመለስ ይጀምራሉ።’

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *