“ካሜራ ፊት ስቀመጥ ዘርም፣ ዘመድም ፓርቲም የለኝም” ቤተልሔም ታፈሰ

Posted by

በቅርቡ በኤልቲቪ ቴሌቪዥን የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀ መንበር ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) ከጋዜጠኛ ቤተልሄም ታፈሰ ያደረጉት ቃለ መጠይቅ አየር ላይ ከዋለ በኋላ የበርካቶች መነጋገሪያ ሆኖ ቆይቷል። ቢቢሲ አማርኛ ከጋዜጠኛ ቤተልሄም ጋር ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ቀርቧል።

ቃለ ምልልሱ ላይ የጋዜጠኝነት ሥነ ምግባርን ጥሻለሁ ብለሽ የምታስቢው ነገር ይኖራል? ከተላለፈ በኋላ ያስተዋልሽው፣ የሕዝብ አስተያየት ከሰማሽ በኋላ ይህን ባልጠይቅ ኖሮ፣ እንደዚህ ማድረግ አልነበረብኝም የምትያቸው ነጥቦች አሉ?

የምፀፀትበት ምንም ነገር የለም። የአብን ሊቀ መንበር ዶ/ር ደሳለኝ የሚያምኑበትን ነገር ነው የተጠየቁት። በገጻቸው ላይ፣ በሪፓርተር ጋዜጣ ላይ ያወጡትን ጥያቄ ነው የተጠየቁት። ጥያቄው አፋጣጭ ባህሪ አለው። መልሱን እስካገኝ ድረስ ወትውቻቸኋለሁ። እሳቸውን ለመጉዳት፣ ‘ፐርሰናሊ’ እሳቸውን ‘አታክ’ ለማድረግ የተደረገ ምንም ነገር አልነበረም። የተጠየቁት ሦስት ጥያቄዎች ነው። የሚያምኑበትን። የጻፉትን። የሚከተሉትን። ዶክተሩም እንደሚያምኑበት አድርገው ነው ያስረዱት። በዛ ጉዳይ ላይ የሚፀፅተኝ ነገር የለም። ከሥነ ምግባር የወጣ ምንም ነገር የለውም። ቢኖረውም ‘ኤዲቶርያል ግሩፑ’ አያሳልፈውም ነበር። በዚህ ልክም መነጋገሪያ መሆን የነበረበት ጉዳይ አልበረም። እስከዛሬ ካደረኩት በጣም ጠንካራ ነው የምለው ከጀዋር መሀመድ ጋር ያደረኩት ቃለ ምልልስ ነው። ከዚኛው ይልቅ በጣም ከባባድ ጥያቄዎች ተጠይቀውበታል ብዬ የማስበው የጀዋርን ነው። ምክንያቱም የጠቅላይ ሚንስትሩን [ጉዳይ] አንስተናል። ማስከሰስ ካለበት እሱ ነበር ሊያስከስሰኝ የሚገባው።

ከአማራ ቲቪ የተወሰደ የአማራ ገበሬዎች እየተወያዩ የሚያሳይ ቪድዮ አቅርበሻል። ተጠያቂው እዛው ባሉበት የቀረበ ቪድዮ መሆን ነበረት የሚል አስተያየት አይቻለሁ።

ቪድዮው ከወጣ በኋላ እኔም ዓይቻለሁ። ግን ይሄ ጉዳይ መነሳት የነበረበት የጀዋር ቃለ መጠይቅ ያለፈ ጊዜም ነበር። ያኔም ማወዛገብ፣ ያኔም ማጨቃጨቅ፣ ያኔም ማነጋገር ነበረበት። ጀዋር ቃለ ምልልስ ላይም እሱን ሳላስፈቅድ ከአራት ቪድዮዎች በላይ ተጠቅሜያለሁ። ያኔም [ጥያቄው] ቢነሳ ጥሩ ነበር። ቪድዮውን እኛ አልሠራነውም፤ አማራ ቴሌቭዥን ነው የሠራው። በግሌ ብሔሩን የሚያዋርድ ምንም ነገር አላደረግኩም። በጣም ተጠንቅቄ ነው የሠራሁት።

ቪድዮውን መላሹ ራሱን መከላከልና ተጨማሪ አስተያየት መስጠት በማይችልበት ሁኔታ መክተት እንግዳውን ማሳጣት አይሆንም? ያንቺን ነጥብ አጉልቶ ለማሳየት ሆን ተብሎ የተደረገ ይመስላል።

መጀመሪያ ላይ ይህንን ቪድዮ መጠቀም የጀመርኩት ጀዋር ላይ ነው። ስለዚህ ያኔም መከሰስ ነበረብኝ ነው የኔ ቅሬታ። እውነት ለመናገር ሆነ ብዬ ዶክተሩን ‘አታክ’ ለማድረግ ምንም አላደረኩም። ሥራዬን ነው የሠራሁት። በዚህ ጉዳይ ላይ ‘ኤዲቶሪያል ግሩፑ’ ቢጠየቅበት ይሻል ይመስለኛል።

ጀዋር ላይ ቪድዮ መጠቀም ይህንን ትክክል ያደርገዋል? ከጀዋር ቃለ መጠይቅ የትኞቹ ጥያቄዎች ናቸው ሊያስጠይቁኝ ይችሉ ነበር የምትይው?

ከኛ ባህል አንጻር ያልተለመዱ ነገሮች ሆነውበታል። ጠንካራ ነበር። የዶክተሩን ያህል እያንዳንዱን ነገር አንድ በአንድ ባንመላለስበትም ከባድ ጥያቄዎችን ነው የተጠየቀው። በተለይ በጠቅላይ ሚንስትሩ ዙሪያ የተሽከረከሩ ጥያቄዎች በዋዛ የሚታዩ አይደሉም። ሌላ ሰው ቢሆን የሚመልሳቸው አይመስለኝም። ሌላ ሰው ቢሆን ቢጠየቅባቸው ምን ይሆናል? አላውቅም። ከዚህ በፊት በዚህ ዓይነት ሁኔታ አንድ ጠቅላይ ሚንስትር ወይም የሀገር መሪ ሚዲያ ላይ ተተችቶ ነበር ወይ? የመጀመሪያው ይመስለኛል። የተፈተንኩበትም ቃለ ምልልስ እሱ ነው።

ብሮድካስት ባለልጣን የጀዋር ላይ ምንም ሳይል እዚ ላይ አስተያየት መስጠቱ ገርሞሻል?

የጀዋር ላይ ብቻ አይደለም። የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽነሩ ቡራዮ በተፈጠረው ግጭት ላይ በጣም ጠንካራ ጥያቄ ተጠይቀዋል። ማወዛገብ ማነጋገር የነበረበት እሱ ነበር። እሳቸውም ተፋጠውበታል። ይህንን ጉዳይ መቀልበስ የፈለጉ ሌሎች ሰዎች ይኖራሉ። ሊገባኝ አልቻለም። በዚህ ልክ መጋጋል የነበረበት ቪድዮ አልነበረም። ከሌሎች ሥራዎቼ አንጻር ምንም የተለየ የተደረገ ነገር የለም።

ለምን ጉዳዩ ይህን ያህል ያነጋጋረ ይመስልሻል?

በግሌ የሚገባኝ ነገር አለ። ግን በግሌ የምተወው ነገር አለ። እንደዚህ እንደዛ ብዬ አልነግርህም።

ጥላሽን የምትሸሺ ሆነሻል እየተባለ ነው። ከቤት ትወጫለሽ? ካፌ እንደልብ ትገብያለሽ?

ድሮውኑም ካፌ የምሔድ ዓይነት አይደለሁም። ረዥም ጊዜዬን በማንበብ ወይም ቤቴ ውስጥ ነው የማሳልፈው። ግን እወጣለሁ። እንቀሳቀሳለሁ፤ ራሴ ነኝ የምነዳው። ምንም የሚያስፈራኝ ነገር የለም። ገዳይ አድብቶ ነው የሚመጣው። ገዳይ እየተናገረ አይመጣም። በግሌ እገደላለሁ የሚል ስጋት የለኝም። ዛቻዎች ግን በተደጋጋሚ ይመጣሉ። ቀንሽን ጠብቂ ይሉኛል።

ከዚ ቃለ ምልልስ በኋላ ያልተኛሽባቸው ለቶች አሉ? አሁን ያለሽበት ሁኔታ ምን ይመስላል?

ፌስቡክ ላይ ቅስቀሳ ተደርጓል። ይሄ አሁን የምትደውልልኝ ስልኬ ተበትኗል። ደውላችሁ ስደቧት የሚል። ስድብ የደረሰብኝ በጾታዬ ነው። ዘሬና ሃይማኖቴም አልቀረም። በእርግጥ በራሴ ላይ መቀለድ ማሾፍ የምወድ ልጅ ነኝ። ቀደም ብሎ የአብን ቃለምልልስ ከመለቀቁ አራት አምስት ቀን ጀምሮ ማስፈራሪያዎች መጥተው ነበር። በከፍተኛ ጥንቃቄ የሠራሁት፣ ምንም ሐሳብ ሳልቆርጥባቸው የሠራሁትም ለዛ ነው። ቀደም ብሎ አየር ላይ ከመዋሉ በፊት የጀመረ ዛቻ ነበር። አንደንዶቹ እስካሁን ስልኬ ላይ ተቀምጠዋል። ያው እንገድልሻለን ነው። ግን የሚያወራ ሰው እንደማይገድል እናውቃለን። ይገድሉኛል ብዬ አልፈራሁም። እንደዚህ ዓይነት ሽብር ውስጥም አልነበርኩም።

ከመተላለፉ በፊት ዛቻ መጀመሩ የተደራጀ ነገር መኖሩን ያመላክት ይሆን?

የግል አስተያየቴ ይሆንብኝና ነገሮችን አንዳልረብሻቸው እፈልጋለሁ። ምንም ዓይነት ጸብና ጥላቻ ውስጥ ከማንም ጋር መግባት የምወድ ሰው አይደለሁም። ኦሮሞ ናት የሚለው ማጥላላት በስፋት ነው የተካሄደው። ግን የአማራን ሕዝብ በዛ ቃለ መጠይቅ አላዋረድኩም። ሕዝቡ ታላቅ ሕዝብ እንደሆነ ነው የተናገርኩት። ከዛ በፊትም ለአማራ ሕዝብ የተከራከርኩባቸው ቪድዮዎች አሉ። ከዶ/ር ዲማ ነገኦ፣ አረጋዊ በርሔ የተደረጉ ቃለ መጠይቆች ስለ አማራ የሚቆረቆሩ ናቸው። ለሕዝቡ ቀና አመለካከት ቢኖረኝም ሥራዬ መጠየቅ ስለሆነ እዛጋ ዶክተሩ የሚያምኑበትን ነገር በተቃራኒው ሆኜ ጠይቄያቸዋለሁ። ይሄ እንዴት ከሌላ ብሔር ጋር ያስማማል የሚለው ሀገር መምራት የሚፈልጉ ሰው ስለሆኑ፣ ፓርቲውም ሀገራዊ ፓርቲ ነው ስላሉ፣ ጥያቄ ጠይቄየአለሁ። ሥራ ነው የሠራሁት። በማኅበር ተደራጅተዋል ወይ? ማለት አልፈግም። ሥራው በራሱ አዲስ ስለሆነ የራሱ ጫናዎች አሉት። እኔ የማስበው እየበረቱ መቀጠልን ነው።

ይህንን ቃለ ምልልስ ወንድ ጋዜጠኛ ቢያደርገው ሌላ መልክ ይኖረዋል?

አሁን አሁን ሴት በመሆኔ ነው ብዬ አስባለሁ። ከዚህ በፊት ቃለ መጠይቅ ስገባ ሴት መሆኔ ትዝ አይለኝም። ጾታዬ ትዝ ብሎኝ አያውቅም። ወንድ የሚያደርገውን ሁሉ ማድረግ እንደምችል አምናለሁ። በቀላሉ እኔን በትናንሽ ምክንያቶች መስደብ ያቆማታል ብለው ከማሰብም ሊሆን ይችላል። ለቃለ መጠይቅ ወንዶች ፊት ለፊት ስቀመጥ እራሴን ሴት ብዬ አስታውሼ አላውቅም። አሁን በግድ እንዳስታውስ እየሆንኩ ነው።

በቤተሰብ ደረጃ መረበሽ አለ?

ቤተሰቦቼ እንደተረበሹ አውቃለሁ። አርሲ ነው የሚኖሩት። እኔም ራሴ የአርሲ ልጅ ነኝ። ቤተሰቦቼ በአካባቢውም የሚወደዱ ሰዎች ናቸው። እነሱ ጋ በቀጥታ የሄደ ነገር የለም። በሰፈራቸው ተከባብረው ተዋደው የሚኖሩ ሰዎች ናቸው። እነሱ ጋ የሄደ ነገር ባይኖርም ለኔ እንደሰጉ ግን አውቃለሁ።

አልፈራሽም ግን?

እኔ በራሴ መቀለድ የምወድ፣ ፈተናዎችን የማልፈራ፣ በድንጋጤ ወደ ኋላ የማልመለስ ግትር የምባል ዓይነት ሰው ነኝ። ጓደኞቼም በቅርበት ያውቃሉ ባህሪዬን። ፍርሃትን የማስተናግድ ሰው አይደለሁም። እንግዲህ የሚመጣም ከሆነ መቀበል ነው፤ የሚመጣ ግን አይመስለኝም በግሌ።

ዕለታዊ የጸሎት ጊዜሽን ጨምረሻል?

(ሳቅ) ሁሌም እጸልያለሁ። የተለየ ጸሎት ግን አልጀመርኩም። አድነኝ ምናምን እስካሁን አላልኩም። ጸሎት ሁልጊዜም አደርጋለሁ። መሞት የምፈራ ሰው አይደለሁም። መሞት ኪሳራ ነው ብዬም አላስብም።

ነገሩ ከፍ ወዳለ ዕውቅና እንደወሰደሽ መረዳት ይቻላል። ይሄ ቃለ መጠይቅ ዝነኛ አድርጎኛል የሚል መልካም ስሜት ተፈጥሮብሻል?

ዝነኛ መሆኔን አላውቅም። በእርግጥ ፌስቡኮችን አያለሁ። የሚጻፉትን፣ ሰዎች ስለኔ የሚሏቸውን ነገሮች ሳይ አንዳንድ ጊዜ እንባዬን ያመጡብኛል። እኔ ምንም ነገር አልሠራሁም። ለአገሬ መሥራት የሚገባኝን እኔ ማድረግ ያለብኝን ገና ምንም አላደረኩም። ገና እየተንደረደርኩ ነው ያለሁት፣ እና በኃያላን ሰዎች መካከል ራሴን ሳገኘው፣ ታላላቅ ሰዎች ስለኔ ሲጽፉ፤ ስለኔ ሲናገሩ በግሌ እምባዬን ያመጣብኛል፤ ግን ዝና የሚለው ነገር ላይ ገና ነው፤ ሕይወቴ ውስጥም እሱ ብዙም የሚያመጣብኝ ተጽእኖ ያለ አይመስለኝም።

ቃለምልልሱ እንደዚህ የሀገር መነጋገሪያ ይሆናል ብለሽ አስበሽ ነበር?

[ቃለ ምልልሶቹ] በየሳምንቱ አነጋጋሪ ሆነው ነው የዘለቁት። በጣም ትንሽ ናቸው ፕሮግራሞቼ። በጣም አጭር ጊዜ ነው። ወደ ሁለት ወር ቢሆነኝ ነው። ግን ባልተለመደ ቀለም ስለመጣ አነጋጋሪ ሆኖ ይቀጥላል። ይህን ያህል የሚያሰድበኝና የሚያዋርደኝ ይሆናል ብዬ ግን አልጠበቅኩም። አንዳንድ በቅርብ ያሉ ወዳጆቼ ግን የሥነ ልቦና ዝግጅት እንዳደርግ ነግረውኝ ነበር። በዚህ ሁኔታ ሰፊ ልምድ ስለነበረኝ ያን ያህል ሳይጎዳኝ ነው ያለፈው። ሃይማኖት አካባቢ እሠራ ነበር። ከፓለቲካው በተሻለ ሃይማኖቱ በጣም ‘ሴንስቲቭ’ ነው። ተመሳሳይ ውግዘቶች ይመጡብኝ ነበር። ጥቂት ወዳጆቼ ሊመጣ የሚችለውን ነገር ነግረውኝ ነበር። እንዳሉኝ ነው የሆነው። እንደ ትንቢት ነው የሆነው። ወዳጆቼ እንጂ እኔ አልጠበቅኩም ነበር። ባልጠብቅም ምንም ማድረግ አይቻልም። እንደዛ ሆኖ አልፏል።

to be continued…

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *