በጋምቤላ ከተማ በተነሳ ግጭት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት አለፈ

Posted by

ከትናንት በስቲያ በጋምቤላ ከተማ በተነሳ ግጭት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት ማለፉንና 21 ሰዎች ለጉዳት መዳረጋቸውን የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ።

አቶ ኦባንግ «ወጣቶቹ የተገደሉት ከፀጥታ ኃይሎች በበተኮሰ ጥይት ነው፤ ጥያቄያቸው ደግሞ የመልካም አስተዳደር ነበር» ይላሉ።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪ ጋትዊች ጋልዋክ የግጭቱን መንስዔ ሲያስረዱ፤ በአኝዋክ እና ኑዌር ወጣቶች መካከል የተነሳ ግርግር ነው ቢሉም፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አቶ ኦባንግ ግን ጉዳዩ የመልካም አስተዳደር ነው፤ ጥያቄውም የቆየ ነው ይላሉ።

«የጋምቤላ ችግር የቆየ፣ የሰነበተ ነው። የክልሉ ነዋሪዎች በተለይ ደግሞ ወጣቶች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ማቅረብ ከጀመሩ ዓመታት አልፈዋል። ነገር ግን ምን ዓይነት መፍትሄ አልመጣም። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደሥልጣን ከመጡ ወዲህም ቢሆን ሌሎች ክልሎች የመልካም አስተዳደር ጥያቄ በማንሳት ምላሽ ሲያገኙ የኛ ግን ተረስቷል» በማለት አቶ ኦባንፍ ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።

የጋምቤላ ከተማ ነዋሪዎች ይህን የመልካም አስተዳደር ጥያቄ ይዘው ሰልፍ የወጡት ሰኞ ዕለት ጠዋት እንደሆነ አቶ ኦባንግ ይናገራሉ።

«ወጣቶቹ ጉዳያቸውን በሰላማዊ መንገድ ነበር ሲያቀርቡ የነበረው» የሚሉት አቶ ኦባንግ «አንድ ጎማ ከማቃጠል በቀር ዱላ አልያዙ፤ ድንጋይ አልወረወሩ» በማተለት የነበረውን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ከዛ በኋላ ግን የፀጥታ ኃይሎች ወደ ሰላማዊ ሰልፈኞቹ መተኮስ እንደጀመሩ ነው አቶ ኦባንግ የሚናገሩት።

«ሰላማዊ ሰልፈኞች ላይ ተኩሱ የሚለው ትዕዛዝ ከየት እንደመጣ ሊጣራ ይገባል» ይላሉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ኦባንግ።

በዚህ ጉዳይ የጋምቤላ ክልል አስተዳደር ያለው ነገር የለም፤ ቢቢሲ የክልሉን ባለስልጣናት ለማነጋጋር ያደረገነው ተደጋጋሚ ሙከራም ሊሳካ አልቻለም።

አቶ ኦባንግ «የክልሉ ፕሬዝደንትን በጉዳዩ ዙሪያ ለማነጋገር ሞክሬ ስልክ ሊነሳልኝ ባለመቻሉ ምላሽ አላገኘሁም» ይላሉ።

የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ አዲስ አበባ በመዝለቅ ስለሁኔታው ከጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጋር እንደተወያዩና ጠ/ሚኒስትሩ «ኃላፊነት እንወስዳለን» እንዳሏቸው ይናገራሉ።

የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ሁኔታውን እንዲያረጋጋና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ እንዲሰጥ፤ እንዲሁም ጥፋት የፈፀሙ እንዲጠየቁ የተቻላቸውን እንደሚያደርጉ ነው አቶ ኦባንግ የሚያብራሩት።

የኃይማኖት አባቶች እና የሃገር ሽማግሌዎች ተባብረው ሁኔታውን ለጊዜው እንዳረጋጉትና አሁን ከተማዋ አንፃራዊ መረጋገት እንደታየባት ማወቅ ችለናል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *