መስቀል በቤተ-ጉራጌ

Posted by

በቤተ- ጉራጌ መስቀል የአንድ ቀን በዓል አይደለም፡፡ ከ10 ቀናት በላይ የሚወስድ ልዩ የፈንጠዝያ ረድፍ እንጂ፡፡

ከመስከረም 12 በፊት የጉራጌ ብሄር ተወላጆች፤ ከመላው የሀገሪቱ ክፍል ወደ ትውልድ ስፍራቸው ይተማሉ፡፡

የዕድሜ ባለጸጋው አቶ ፍቃዱ ካሶሬ እንደሚያምኑት፤ ከወጣቶች በሰው እስከሚደገፉ አዛውንቶች ድረስ የመስቀል ሰሞን ሀገር ቤት የመግባታቸው ነገር አያጠያቅም፡፡ በዚያ ሰሞን በጉራጌዎች የንግድ ተሳትፎ ፈክታ የከረመችው አዲስ አበባ ጭርታ ይመታታል፡፡

‹‹አሁን በዚህ ሰሞን መርካቶ ብትሄድ፣ የተወረረ ቦታ መስሎ ታገኘዋለህ›› ይላሉ እሳቸው ሁኔታውን ሲስሉት፡፡

ልጃቸው መሳይ ፈቃዱን ጨምሮ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የብሄረሰቡ ተወላጆች ወደ ቀያቸው አቅንተዋል፡፡ ምክንያቱም መስቀል በጉራጌ ሃይማኖታዊ በዓል፣ የመተጫጫ ወቅት፣ የእርቅ እና የአንድነት አውድ ስለሆነ በመሳይ አገላለጽ ‹‹መች በደረሰ የሚያስብል ወቅት›› ነውና፡፡

ከወሬት ያህናእስከ አዳብና

አቶ ፈቃዱ ካሶሬ እንዳወጉን፤ መስከረም 13 ወሬት ያህና በተሰኘው የበዓል መክፈቻ መሰናዶ ሰሞነ መስቀል ይጀመራል፡፡ ወሬት ያህና ጉጉት እና ናፍቆት የፈጠረውን እንቅልፍ አልባ ቀን የሚዘክር ቃል ነው፡፡

መስከረም 14 የእርድ ዋዜማ ሲሆን የልጆች የደመራ ፣ የሴቶች የአይቤ እና ጎመን ቀን ይባላል፡፡ ቤቶች የሚሰነዳዱበት የእንፋሎት ቆጮ የሚቀርብበት ቀንም ነው፡፡

መስከረም 15 ዋናው የጉራጌ የመስቀል በዓል (ወኀምያ ) ነው፡፡ በዚህ ዕለት እርድ ይፈጸማል፡፡ መስከረም 16 ምግይር ወይም ደመራ የሚባለው ቀን ነው (የአባቶች ደመራም ይባላል)፡፡

በየቤቱ፤ ጠዋት የህጻናት ማታ ደግሞ የአባቶች ደመራ ይለኮሳል፡፡ በዚህ ዕለት ከብቶች ከቤት አይወጡም፡፡

መስከረም 17 ንቅባር ወይንም ትልቁ በዓል ነው፡፡ ዘመድ አዝማድ ሻኛ አስመርቆ በጋራ የሚቋደስበት፣ ጎረቤት በአንድ ሆኖ ሲስቅ ሲያወካ የሚውልበት የማህበረሰብ መሰብሰቢያ ቀን ነው፡፡

ከመስከረም 18 እስከ 23 የጀውጀው የሚባለው ስርዓት ይቀጥላል፡፡ የጀውጀው የመተያያ ቀን ሲሆን ባለትዳሮች ስጦታ እና መመረቂያ ይዘው የወላጆቻቸውን ቤት በማቅናት የሚጠይቁበት ነው፡፡

የመዝጊው በዓል አዳብና ይባላል፡፡ አዳብና ጎረምሶች እና ልጃገረዶች የጭፈራ ችሎታቸውን የሚያሳዩበት፤ የወደፊት የትዳር ተጣማሪያቸውን የሚያዩበት፣ የሚያጩበት በዓል ነው፡፡ ጭፈራው ለተወሰኑ ቀናትን ሊቀጥል ይችላል፡፡

የአቶ ፈቃዱ ካሶሪ ልጅ፤ ባህሉ በሚፈቅደው መንገድ ካጨና ካገባ ዘንድሮ አንድ ዓመት እንደደፈነ ይናገራል፡፡ እንግዲህ መስቀል በሚመጣ ጊዜ ‹‹ለእኔ ድርብ በዓል ነው›› ብሎናል፡፡

የዓመት ሰው ይበለን

ወደ ሁለት ሚሊየን የሚገመቱ የብሄረሰቡ አባላት እንደሚሳተፉበት የሚነገረው በዓል የሚያካትታቸው ክንውኖች ካለ ምርቃት እና መልካም ምኞቶች አይደመደሙም፡፡

የዕድሜ ባለጸጎች ‹‹የሀገራችንን ዳር ዳር ለጠላት እሳት፤ ለህዝቦቿ መሃሏን ገነት ያድርግልን›› ከሚለው ምርቃት ጀምሮ፤ ሰው፣ ከብቱ፣ ጋራ እና ሸንተረሩ ሰላም እና ልምላሜ፣ በረከት እና ጸጋ እንዳይለየው ይመረቃል፡፡

ታዳሚውም የአባቶችን ምርቃት እየተከተለ ‹‹አሜን!›› ይላል፡፡ የዓመት ሰው ይበለን- አሜን!

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *